የያዕቆብ ፡ መልእክት - ምዕራፍ ፫ (James - Chapter 3)

From WikiMezmur, the free amharic mezmur lyrics database.
ዘልለው ለመሔድ፦ የማውጫ ቁልፎች, ፍለጋ


፩፡ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ ከእናንተ ፡ ብዙዎቹ ፡ አስተማሪዎች ፡ አይሁኑ ፥ የባሰውን ፡ ፍርድ ፡ እንድንቀበል ፡ ታውቃላችሁና። ፪፡ ሁላችን ፡ በብዙ ፡ ነገር ፡ እንሰናከላለንና ፤ በቃል ፡ የማይሰናከል ፡ ማንም ፡ ቢኖር ፡ እርሱ ፡ ሥጋውን ፡ ሁሉ ፡ ደግሞ ፡ ሊገታ ፡ የሚችል ፡ ፍጹም ፡ ሰው ፡ ነው። ፫፡ እነሆ ፥ ፈረሶች ፡ ይታዘዙልን ፡ ዘንድ ፡ ልጓም ፡ በአፋቸው ፡ ውስጥ ፡ እናገባለን ፥ ሥጋቸውንም ፡ ሁሉ ፡ እንመራለን። ፬፡ እነሆ ፥ መርከቦች ፡ ደግሞ ፡ ይህን ፡ ያህል ፡ ታላቅ ፡ ቢሆኑ ፡ በዐውሎ ፡ ነፋስም ፡ ቢነዱ ፥ የመሪ ፡ ፈቃድ ፡ ወደሚወደው ፡ ስፍራ ፡ እጅግ ፡ ታናሽ ፡ በሆነ ፡ መቅዘፊያ ፡ ይመራሉ። ፭፡ እንዲሁም ፡ አንደበት ፡ ደግሞ ፡ ትንሽ ፡ ብልት ፡ ሆኖ ፡ በታላላቅ ፡ ነገር ፡ ይመካል። እነሆ ፥ ትንሽ ፡ እሳት ፡ እንዴት ፡ ያለ ፡ ትልቅ ፡ ጫካ ፡ ያቃጥላል። ፮፡ አንደበትም ፡ እሳት ፡ ነው። አንደበት ፡ በብልቶቻችን ፡ መካከል ፡ ዓመፀኛ ፡ ዓለም ፡ ሆኖአል ፤ ሥጋን ፡ ሁሉ ፡ ያሳድፋልና ፥ የፍጥረትንም ፡ ሩጫ ፡ ያቃጥላል ፥ በገሃነምም ፡ ይቃጠላል። ፯፡ የአራዊትና ፡ የወፎች ፡ የተንቀሳቃሾችና ፡ በባሕር ፡ ያለ ፡ የፍጥረት ፡ ወገን ፡ ሁሉ ፡ በሰው ፡ ይገራል ፥ ደግሞ ፡ ተገርቶአል ፤ ፰፡ ነገር ፡ ግን ፡ አንደበትን ፡ ሊገራ ፡ ማንም ፡ ሰው ፡ አይችልም ፤ የሚገድል ፡ መርዝ ፡ የሞላበት ፡ ወላዋይ ፡ ክፋት ፡ ነው። ፱፡ በእርሱ ፡ ጌታንና ፡ አብን ፡ እንባርካለን ፤ በእርሱም ፡ እንደ ፡ እግዚአብሔር ፡ ምሳሌ ፡ የተፈጠሩትን ፡ ሰዎች ፡ እንረግማለን ፤ ፲፡ ከአንድ ፡ አፍ ፡ በረከትና ፡ መርገም ፡ ይወጣሉ። ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ ይህ ፡ እንዲህ ፡ ሊሆን ፡ አይገባም። ፲፩፡ ምንጭስ ፡ ከአንድ ፡ አፍ ፡ የሚጣፍጥንና ፡ የሚመርን ፡ ውኃ ፡ ያመነጫልን ? ፲፪፡ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ በለስ ፡ ወይራን ፡ ወይስ ፡ ወይን ፡ በለስን ፡ ልታፈራ ፡ ትችላለችን ? ከጨው ፡ ውኃም ፡ ጣፋጭ ፡ ውኃ ፡ አይወጣም። ፲፫፡ ከእናንተ ፡ ጥበበኛና ፡ አስተዋይ ፡ ማን ፡ ነው ? በመልካም ፡ አንዋዋሩ ፡ ስራውን ፡ በጥበብ ፡ የዋህነት ፡ ያሳይ። ፲፬፡ ነገር ፡ ግን ፡ መራራ ፡ ቅንዓትና ፡ አድመኛነት ፡ በልባችሁ ፡ ቢኖርባችሁ ፥ አትመኩ ፡ በእውነትም ፡ ላይ ፡ አትዋሹ። ፲፭፡ ይህ ፡ ጥበብ ፡ ከላይ ፡ የሚወርድ ፡ አይደለም ፤ ነገር ፡ ግን ፡ የምድር ፡ ነው ፥ የሥጋም ፡ ነው ፥ የአጋንንትም ፡ ነው ፤ ፲፮፡ ቅንዓትና ፡ አድመኛነት ፡ ባሉበት ፡ ስፍራ ፡ በዚያ ፡ ሁከትና ፡ ክፉ ፡ ስራ ፡ ሁሉ ፡ አሉና። ፲፯፡ ላይኛይቱ ፡ ጥበብ ፡ ግን ፡ በመጀመሪያ ፡ ንጽሕት ፡ ናት ፥ በኋላም ፡ ታራቂ ፥ ገር ፥ እሺ ፡ ባይ ፡ ምሕረትና ፡ በጎ ፡ ፍሬ ፡ የሞላባት ፥ ጥርጥርና ፡ ግብዝነት ፡ የሌለባት ፡ ናት። ፲፰፡ የጽድቅም ፡ ፍሬ ፡ ሰላምን ፡ ለሚያደርጉት ፡ ሰዎች ፡ በሰላም ፡ ይዘራል።













Navigation menu

MediaWiki spam blocked by CleanTalk.