የያዕቆብ ፡ መልእክት - ምዕራፍ ፬ (James - Chapter 4)

From WikiMezmur, the free amharic mezmur lyrics database.
ዘልለው ለመሔድ፦ የማውጫ ቁልፎች, ፍለጋ


፩፡ በእናንተ ፡ ዘንድ ፡ ጦርና ፡ ጠብ ፡ ከወዴት ፡ ይመጣሉ ? በብልቶቻችሁ ፡ ውስጥ ፡ ከሚዋጉ ፡ ከእነዚህ ፡ ከምቾቶቻችሁ ፡ አይደሉምን ? ፪፡ ትመኛላችሁ ፡ ለእናንተም ፡ አይሆንም ፤ ትገድላላችሁ ፡ በብርቱም ፡ ትፈልጋላችሁ ፥ ልታገኙም ፡ አትችሉም ፤ ትጣላላችሁ ፡ ትዋጉማላችሁ ፡ ነገር ፡ ግን ፡ አትለምኑምና ፡ ለእናንተ ፡ አይሆንም ፤ ፫፡ ትለምናላችሁ ፥ በምቾቶቻችሁም ፡ ትከፍሉ ፡ ዘንድ ፡ በክፉ ፡ ትለምናላችሁና ፡ አትቀበሉም። ፬፡ አመንዝሮች ፡ ሆይ ፥ ዓለምን ፡ መውደድ ፡ ለእግዚአብሔር ፡ ጥል ፡ እንዲሆን ፡ አታውቁምን ? እንግዲህ ፡ የዓለም ፡ ወዳጅ ፡ ሊሆን ፡ የሚፈቅድ ፡ ሁሉ ፡ የእግዚአብሔር ፡ ጠላት ፡ ሆኖአል። ፭፡ ወይስ ፡ መጽሐፍ። በእኛ ፡ ዘንድ ፡ ያሳደረው ፡ መንፈስ ፡ በቅንዓት ፡ ይመኛል ፡ ያለው ፡ በከንቱ ፡ እንደ ፡ ተናገረ ፡ ይመስላችኋልን ? ፮፡ ነገር ፡ ግን ፡ ጸጋን ፡ አብልጦ ፡ ይሰጣል ፤ ስለዚህ። እግዚአብሔር ፡ ትዕቢተኞችን ፡ ይቃወማል ፥ ለትሑታን ፡ ግን ፡ ጸጋን ፡ ይሰጣል ፡ ይላል። ፯፡ እንግዲህ ፡ ለእግዚአብሔር ፡ ተገዙ ፤ ዲያብሎስን ፡ ግን ፡ ተቃወሙ ፡ ከእናንተም ፡ ይሸሻል ፤ ፰፡ ወደ ፡ እግዚአብሔር ፡ ቅረቡ ፡ ወደ ፡ እናንተም ፡ ይቀርባል። እናንተ ፡ ኃጢአተኞች ፥ እጆቻችሁን ፡ አንጹ ፤ ሁለት ፡ አሳብም ፡ ያላችሁ ፡ እናንተ ፥ ልባችሁን ፡ አጥሩ። ፱፡ ተጨነቁና ፡ እዘኑ ፡ አልቅሱም ፤ ሳቃችሁ ፡ ወደ ፡ ኀዘን ፡ ደስታችሁም ፡ ወደ ፡ ትካዜ ፡ ይለወጥ። ፲፡ በጌታ ፡ ፊት ፡ ራሳችሁን ፡ አዋርዱ ፡ ከፍ ፡ ከፍም ፡ ያደርጋችኋል። ፲፩፡ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ እርስ ፡ በርሳችሁ ፡ አትተማሙ። ወንድሙን ፡ የሚያማ ፡ በወንድሙም ፡ የሚፈርድ ፡ ሕግን ፡ ያማል ፡ በሕግም ፡ ይፈርዳል ፤ በሕግም ፡ ብትፈርድ ፡ ፈራጅ ፡ ነህ ፡ እንጂ ፡ ሕግን ፡ አድራጊ ፡ አይደለህም። ፲፪፡ ሕግን ፡ የሚሰጥና ፡ የሚፈርድ ፡ አንድ ፡ ነው ፤ እርሱም ፡ ሊያድን ፡ ሊያጠፋም ፡ የሚችል ፡ ነው ፤ በሌላው ፡ ግን ፡ የምትፈርድ ፡ አንተ ፡ ማን ፡ ነህ ? ፲፫፡ አሁንም። ዛሬ ፡ ወይም ፡ ነገ ፡ ወደዚህ ፡ ከተማ ፡ እንሄዳለን ፡ በዚያም ፡ ዓመት ፡ እንኖራለን ፡ እንነግድማለን ፡ እናተርፍማለን ፡ የምትሉ ፡ እናንተ ፥ ተመልከቱ ፥ ነገ ፡ የሚሆነውን ፡ አታውቁምና። ፲፬፡ ሕይወታችሁ ፡ ምንድር ፡ ነው ? ጥቂት ፡ ጊዜ ፡ ታይቶ ፡ ኋላ ፡ እንደሚጠፋ ፡ እንፍዋለት ፡ ናችሁና። ፲፭፡ በዚህ ፡ ፈንታ። ጌታ ፡ ቢፈቅድ ፡ ብንኖርም ፡ ይህን ፡ ወይም ፡ ያን ፡ እናደርጋለን ፡ ማለት ፡ ይገባችኋል። ፲፮፡ አሁን ፡ ግን ፡ በትዕቢታችሁ ፡ ትመካላችሁ ፤ እንደዚህ ፡ ያለ ፡ ትምክህት ፡ ሁሉ ፡ ክፉ ፡ ነው። ፲፯፡ እንግዲህ ፡ በጎ ፡ ለማድረግ ፡ አውቆ ፡ ለማይሠራው ፡ ኃጢአት ፡ ነው።













Navigation menu

MediaWiki spam blocked by CleanTalk.