የያዕቆብ ፡ መልእክት - ምዕራፍ ፪ (James - Chapter 2)

From WikiMezmur, the free amharic mezmur lyrics database.
ዘልለው ለመሔድ፦ የማውጫ ቁልፎች, ፍለጋ


፩፡ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ በክብር ፡ ጌታ ፡ በጌታችን ፡ በኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ፡ ያለውን ፡ እምነት ፡ ለሰው ፡ ፊት ፡ በማድላት ፡ አትያዙ። ፪፡ የወርቅ ፡ ቀለበት ፡ ያደረገና ፡ የጌጥ ፡ ልብስ ፡ የለበሰ ፡ ሰው ፡ ወደ ፡ ጉባኤአችሁ ፡ ቢገባ ፥ እድፍ ፡ ልብስም ፡ የለበሰ ፡ ድሀ ፡ ሰው ፡ ደግሞ ፡ ቢገባ ፥ ፫፡ የጌጥ ፡ ልብስም ፡ የለበሰውን ፡ ተመልክታችሁ። አንተስ ፡ በዚህ ፡ በመልካም ፡ ስፍራ ፡ ተቀመጥ ፡ ብትሉት ፥ ድሀውንም። አንተስ ፡ ወደዚያ ፡ ቁም ፡ ወይም ፡ ከእግሬ ፡ መረገጫ ፡ በታች ፡ ተቀመጥ ፡ ብትሉት ፥ ራሳችሁን ፡ መለያየታችሁ ፡ አይደለምን ? ፬፡ ክፉ ፡ አሳብ ፡ ያላቸውም ፡ ዳኞች ፡ መሆናችሁ ፡ አይደለምን ? ፭፡ የተወደዳችሁ ፡ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ ስሙ ፤ እግዚአብሔር ፡ በእምነት ፡ ባለ ፡ ጠጎች ፡ እንዲሆኑ ፡ ለሚወዱትም ፡ ተስፋ ፡ ስለ ፡ እርሱ ፡ የሰጣቸውን ፡ መንግሥት ፡ እንዲወርሱ ፡ የዚህን ፡ ዓለም ፡ ድሆች ፡ አልመረጠምን ? ፮፡ እናንተ ፡ ግን ፡ ድሆችን ፡ አዋረዳችሁ። ባለ ፡ ጠጎቹ ፡ የሚያስጨንቁአችሁ ፡ አይደሉምን ? ወደ ፡ ፍርድ ፡ ቤትም ፡ የሚጎትቱአችሁ ፡ እነርሱ ፡ አይደሉምን ? ፯፡ የተጠራችሁበትን ፡ መልካሙን ፡ ስም ፡ የሚሰድቡ ፡ እነርሱ ፡ አይደሉምን ? ፰፡ ነገር ፡ ግን ፡ መጽሐፍ። ባልንጀራህን ፡ እንደ ፡ ራስህ ፡ ውደድ ፡ እንደሚል ፡ የንጉሥን ፡ ሕግ ፡ ብትፈጽሙ ፡ መልካም ፡ ታደርጋላችሁ ፤ ፱፡ ለሰው ፡ ፊት ፡ ግን ፡ ብታደሉ ፡ ኃጢአትን ፡ ትሠራላችሁ ፥ ሕግም ፡ እንደ ፡ ተላላፊዎች ፡ ይወቅሳችኋል። ፲፡ ሕግን ፡ ሁሉ ፡ የሚጠብቅ ፥ ነገር ፡ ግን ፡ በአንዱ ፡ የሚሰናከል ፡ ማንም ፡ ቢኖር ፡ በሁሉ ፡ በደለኛ ፡ ይሆናል ፤ አታመንዝር ፡ ያለው ፡ ደግሞ። አትግደል ፡ ብሎአልና ፤ ፲፩፡ ባታመነዝርም ፥ ነገር ፡ ግን ፡ ብትገድል ፥ ሕግን ፡ ተላላፊ ፡ ሆነሃል። ፲፪፡ በነጻነት ፡ ሕግ ፡ ፍርድን ፡ ይቀበሉ ፡ ዘንድ ፡ እንዳላቸው ፡ ሰዎች ፡ እንዲህ ፡ ተናገሩ ፥ እንዲህም ፡ አድርጉ። ፲፫፡ ምሕረትን ፡ ለማያደርግ ፡ ምሕረት ፡ የሌለበት ፡ ፍርድ ፡ ይሆናልና ፤ ምሕረትም ፡ በፍርድ ፡ ላይ ፡ ይመካል። ፲፬፡ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ እምነት ፡ አለኝ ፡ የሚል ፥ ሥራ ፡ ግን ፡ የሌለው ፡ ሰው ፡ ቢኖር ፡ ምን ፡ ይጠቅመዋል ? እምነቱስ ፡ ሊያድነው ፡ ይችላልን ? ፲፭፡ ወንድም ፡ ወይም ፡ እኅት ፡ ራቁታቸውን ፡ ቢሆኑ ፡ የዕለት ፡ ምግብንም ፡ ቢያጡ ፥ ፲፮፡ ከእናንተ ፡ አንዱም። በደኅና ፡ ሂዱ ፥ እሳት ፡ ሙቁ ፥ ጥገቡም ፡ ቢላቸው ፡ ለሰውነት ፡ ግን ፡ የሚያስፈልጉትን ፡ ባትሰጡአቸው ፡ ምን ፡ ይጠቅማቸዋል ? ፲፯፡ እንደዚሁም ፡ ሥራ ፡ የሌለው ፡ እምነት ፡ ቢኖር ፡ በራሱ ፡ የሞተ ፡ ነው። ፲፰፡ ነገር ፡ ግን ፡ አንድ ፡ ሰው። አንተ ፡ እምነት ፡ አለህ ፡ እኔም ፡ ሥራ ፡ አለኝ ፤ እምነትህን ፡ ከሥራህ ፡ ለይተህ ፡ አሳየኝ ፥ እኔም ፡ እምነቴን ፡ በሥራዬ ፡ አሳይሃለሁ ፡ ይላል። ፲፱፡ እግዚአብሔር ፡ አንድ ፡ እንደ ፡ ሆነ ፡ አንተ ፡ ታምናለህ ፤ መልካም ፡ ታደርጋለህ ፤ አጋንንት ፡ ደግሞ ፡ ያምናሉ ፡ ይንቀጠቀጡማል። ፳፡ አንተ ፡ ከንቱ ፡ ሰው ፥ እምነት ፡ ከሥራ ፡ ተለይቶ ፡ የሞተ ፡ መሆኑን ፡ ልታውቅ ፡ ትወዳለህን ? ፳፩፡ አባታችን ፡ አብርሃም ፡ ልጁን ፡ ይስሐቅን ፡ በመሠዊያው ፡ ባቀረበ ፡ ጊዜ ፡ በሥራ ፡ የጸደቀ ፡ አልነበረምን ? ፳፪፡ እምነት ፡ ከሥራው ፡ ጋር ፡ አብሮ ፡ ያደርግ ፡ እንደ ፡ ነበረ ፥ በሥራም ፡ እምነት ፡ እንደ ፡ ተፈጸመ ፡ ትመለከታለህን ? ፳፫፡ መጽሐፍም። አብርሃምም ፡ እግዚአብሔርን ፡ አመነ ፡ ጽድቅም ፡ ሆኖ ፡ ተቈጠረለት ፡ ያለው ፡ ተፈጸመ ፤ የእግዚአብሔርም ፡ ወዳጅ ፡ ተባለ። ፳፬፡ ሰው ፡ በእምነት ፡ ብቻ ፡ ሳይሆን ፡ በሥራ ፡ እንዲጸድቅ ፡ ታያላችሁ። ፳፭፡ እንደዚሁም ፡ ጋለሞታይቱ ፡ ረዓብ ፡ ደግሞ ፡ መልእክተኞቹን ፡ ተቀብላ ፡ በሌላ ፡ መንገድ ፡ በሰደደቻቸው ፡ ጊዜ ፡ በሥራ ፡ አልጸደቀችምን ? ፳፮፡ ከነፍስ ፡ የተለየ ፡ ሥጋ ፡ የሞተ ፡ እንደ ፡ ሆነ ፡ እንዲሁ ፡ ደግሞ ፡ ከሥራ ፡ የተለየ ፡ እምነት ፡ የሞተ ፡ ነው።









Navigation menu

MediaWiki spam blocked by CleanTalk.