፩ኛ ፡ ወደ ፡ ተሰሎንቄ ፡ ሰዎች - ምዕራፍ ፭ (1st Thesallonians - Chapter 5)

From WikiMezmur, the free amharic mezmur lyrics database.
ዘልለው ለመሔድ፦ የማውጫ ቁልፎች, ፍለጋ


፩፡ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ ስለ ፡ ዘመናትና ፡ ስለ ፡ ወራት ፡ ምንም ፡ እንዲጻፍላችሁ ፡ አያስፈልጋችሁም ፤ ፪፡ የጌታ ፡ ቀን ፥ ሌባ ፡ በሌሊት ፡ እንደሚመጣ ፥ እንዲሁ ፡ ይመጣ ፡ ዘንድ ፡ ራሳችሁ ፡ አጥብቃችሁ ፡ አውቃችኋልና። ፫፡ ሰላምና ፡ ደኅንነት ፡ ነው ፡ ሲሉ ፡ ያን ፡ ጊዜ ፡ ምጥ ፡ እርጕዝን ፡ እንደሚይዛት ፡ ጥፋት ፡ በድንገት ፡ ይመጣባቸዋል ፡ ከቶም ፡ አያመልጡም። ፬፡ እናንተ ፡ ግን ፥ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ ቀኑ ፡ እንደ ፡ ሌባ ፡ ይደርስባችሁ ፡ ዘንድ ፡ በጨለማ ፡ አይደላችሁም ፥ ፭፡ ሁላችሁ ፡ የብርሃን ፡ ልጆች ፡ የቀንም ፡ ልጆች ፡ ናችሁና። እኛ ፡ ከሌሊት ፡ ወይም ፡ ከጨለማ ፡ አይደለንም ፤ ፮፡ እንግዲያስ ፡ እንንቃ ፡ በመጠንም ፡ እንኑር ፡ እንጂ ፡ እንደ ፡ ሌሎች ፡ አናንቀላፋ። ፯፡ የሚያንቀላፉ ፡ በሌሊት ፡ ያንቀላፋሉና ፥ የሚሰክሩም ፡ በሌሊት ፡ ይሰክራሉና ፤ ፰፡ እኛ ፡ ግን ፡ ከቀን ፡ ስለ ፡ ሆንን ፥ የእምነትንና ፡ የፍቅርን ፡ ጥሩር ፡ የመዳንንም ፡ ተስፋ ፡ እንደ ፡ ራስ ፡ ቁር ፡ እየለበስን ፡ በመጠን ፡ እንኑር ፤ ፱፡ እግዚአብሔር ፡ ለቍጣ ፡ አልመረጠንምና ፥ በጌታችን ፡ በኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ፡ መዳንን ፡ ለማግኘት ፡ ነው ፡ እንጂ። ፲፡ የምንነቃም ፡ ብንሆን ፥ የምናንቀላፋም ፡ ብንሆን ፥ ከእርሱ ፡ ጋር ፡ አብረን ፡ በሕይወት ፡ እንኖር ፡ ዘንድ ፡ ስለ ፡ እኛ ፡ ሞተ። ፲፩፡ ስለዚህ ፡ እናንተ ፡ ደግሞ ፡ እንደምታደርጉ ፥ እርስ ፡ በርሳችሁ ፡ ተመካከሩ ፡ አንዱም ፡ አንዱም ፡ ሌላውን ፡ ያንጸው። ፲፪፡ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ በመካከላችሁ ፡ የሚደክሙትን ፡ በጌታም ፡ የሚገዙአችሁን ፡ የሚገሥጹአችሁንም ፡ ታውቁ ፡ ዘንድ ፥ ስለ ፡ ሥራቸውም ፡ በፍቅር ፡ ከመጠን ፡ ይልቅ ፡ ታከብሩአቸው ፡ ዘንድ ፡ እንለምናችኋለን። እርስ ፡ በርሳችሁ ፡ በሰላም ፡ ሁኑ። ፲፫፡ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ እንመክራችኋለን ፤ ያለ ፡ ሥርዓት ፡ የሚሄዱትን ፡ ገሥጹአቸው ፤ ድፍረት ፡ የሌላቸውን ፡ አጽኑአቸው ፤ ለደካሞች ፡ ትጉላቸው ፤ ሰውን ፡ ሁሉ ፡ ታገሡ። ፲፬፡ ማንም ፡ ለሌላው ፡ በክፉ ፡ ፈንታ ፡ ክፉ ፡ እንዳይመልስ ፡ ተጠንቀቁ ፥ ነገር ፡ ግን ፡ ሁልጊዜ ፡ እርስ ፡ በርሳችሁ ፡ ለሁሉም ፡ መልካሙን ፡ ለማድረግ ፡ ትጉ። ፲፭፡ ሁልጊዜ ፡ ደስ ፡ ይበላችሁ ፤ ፲፮፡ ሳታቋርጡ ፡ ጸልዩ ፤ በሁሉ ፡ አመስግኑ ፤ ይህ ፡ የእግዚአብሔር ፡ ፈቃድ ፡ በክርስቶስ ፡ ኢየሱስ ፡ ወደ ፡ እናንተ ፡ ነውና። ፲፯፡ መንፈስን ፡ አታጥፉ ፤ ፲፰፡ ትንቢትን ፡ አትናቁ ፤ ሁሉን ፡ ፈትኑ ፡ መልካሙንም ፡ ያዙ ፤ ፲፱፡ ከማናቸውም ፡ ዓይነት ፡ ክፉ ፡ ነገር ፡ ራቁ። ፳፡ የሰላምም ፡ አምላክ ፡ ራሱ ፡ ሁለንተናችሁን ፡ ይቀድስ ፤ መንፈሳችሁም ፡ ነፍሳችሁም ፡ ሥጋችሁም ፡ ጌታችን ፡ ኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ፡ በመጣ ፡ ጊዜ ፡ ያለ ፡ ነቀፋ ፡ ፈጽመው ፡ ይጠበቁ። ፳፩፡ የሚጠራችሁ ፡ የታመነ ፡ ነው ፥ እርሱም ፡ ደግሞ ፡ ያደርገዋል። ፳፪፡ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ ስለ ፡ እኛ ፡ ጸልዩ። ፳፫፡ ከወንድሞች ፡ ሁሉ ፡ ጋር ፡ በተቀደሰ ፡ አሳሳም ፡ ሰላምታ ፡ ተሰጣጡ። ፳፬፡ ይህ ፡ መልእክት ፡ ለቅዱሳን ፡ ወንድሞች ፡ ሁሉ ፡ እንዲነበብ ፡ በጌታ ፡ አምላችኋለሁ። ፳፭፡ የጌታችን ፡ የኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ፡ ጸጋ ፡ ከእናንተ ፡ ጋር ፡ ይሁን ፤ አሜን።









Navigation menu

MediaWiki spam blocked by CleanTalk.