የያዕቆብ ፡ መልእክት - ምዕራፍ ፩ (James - Chapter 1)

From WikiMezmur, the free amharic mezmur lyrics database.
ዘልለው ለመሔድ፦ የማውጫ ቁልፎች, ፍለጋ


፩፡ የእግዚአብሔርና ፡ የጌታ ፡ የኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ፡ ባሪያ ፡ ያዕቆብ ፡ ለተበተኑ ፡ ለአሥራ ፡ ሁለቱ ፡ ወገኖች ፤ ሰላም ፡ ለእናንተ ፡ ይሁን። ፪፡ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ የእምነታችሁ ፡ መፈተን ፡ ትዕግሥትን ፡ እንዲያደርግላችሁ ፡ አውቃችሁ ፥ ልዩ ፡ ልዩ ፡ ፈተና ፡ ሲደርስባችሁ ፡ እንደ ፡ ሙሉ ፡ ደስታ ፡ ቍጠሩት ፡ ፫፡ ትዕግሥትም ፡ ምንም ፡ የሚጎድላችሁ ፡ ሳይኖር ፡ ፍጹማንና ፡ ምሉዓን ፡ ትሆኑ ፡ ዘንድ ፡ ሥራውን ፡ ይፈጽም። ፬፡ ከእናንተ ፡ ግን ፡ ማንም ፡ ጥበብ ፡ ቢጎድለው ፥ ሳይነቅፍ ፡ በልግስና ፡ ለሁሉ ፡ የሚሰጠውን ፡ እግዚአብሔርን ፡ ይለምን ፥ ለእርሱም ፡ ይሰጠዋል። ፭፡ ነገር ፡ ግን ፡ በምንም ፡ ሳይጠራጠር ፡ በእምነት ፡ ይለምን ፤ የሚጠራጠር ፡ ሰው ፡ በነፋስ ፡ የተገፋና ፡ የተነቃነቀ ፡ የባሕርን ፡ ማዕበል ፡ ይመስላልና። ፮፡ ሁለት ፡ አሳብ ፡ ላለው ፡ በመንገዱም ፡ ሁሉ ፡ ለሚወላውል ፡ ለዚያ ፡ ሰው ፡ ከጌታ ፡ ዘንድ ፡ አንዳች ፡ እንዲያገኝ ፡ አይምሰለው። ፯፡ የተዋረደው ፡ ወንድም ፡ ግን ፡ በከፍታው ፥ ባለ ፡ ጠጋም ፡ በውርደቱ ፡ ይመካ ፤ እንደ ፡ ሣር ፡ አበባ ፡ ያልፋልና። ፰፡ ፀሐይ ፡ ከትኵሳት ፡ ጋር ፡ ይወጣልና ፥ ሣርንም ፡ ያጠወልጋልና ፥ አበባውም ፡ ይረግፋልና ፥ የመልኩም ፡ ውበት ፡ ይጠፋልና ፤ እንዲሁ ፡ ደግሞ ፡ ባለ ፡ ጠጋው ፡ በመንገዱ ፡ ይዝላል። ፱፡ በፈተና ፡ የሚጸና ፡ ሰው ፡ የተባረከ ፡ ነው ፤ ከተፈተነ ፡ በኋላ ፡ ለሚወዱት ፡ ተስፋ ፡ ስለ ፡ እርሱ ፡ የሰጣቸውን ፡ የሕይወትን ፡ አክሊል ፡ ይቀበላልና። ፲፡ ማንም ፡ ሲፈተን። በእግዚአብሔር ፡ እፈተናለሁ ፡ አይበል ፤ እግዚአብሔር ፡ በክፉ ፡ አይፈተንምና ፤ እርሱ ፡ ራሱስ ፡ ማንንም ፡ አይፈትንም። ፲፩፡ ነገር ፡ ግን ፡ እያንዳንዱ ፡ በራሱ ፡ ምኞት ፡ ሲሳብና ፡ ሲታለል ፡ ይፈተናል። ፲፪፡ ከዚህ ፡ በኋላ ፡ ምኞት ፡ ፀንሳ ፡ ኃጢአትን ፡ ትወልዳለች ፤ ኃጢአትም ፡ ካደገች ፡ በኋላ ፡ ሞትን ፡ ትወልዳለች። ፲፫፡ የተወደዳችሁ ፡ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ አትሳቱ። ፲፬፡ በጎ ፡ ስጦታ ፡ ሁሉ ፡ ፍጹምም ፡ በረከት ፡ ሁሉ ፡ ከላይ ፡ ናቸው ፥ መለወጥም ፡ በእርሱ ፡ ዘንድ ፡ ከሌለ ፡ በመዞርም ፡ የተደረገ ፡ ጥላ ፡ በእርሱ ፡ ዘንድ ፡ ከሌለ ፡ ከብርሃናት ፡ አባት ፡ ይወርዳሉ። ፲፭፡ ለፍጥረቱ ፡ የበኵራት ፡ ዓይነት ፡ እንድንሆን ፡ በእውነት ፡ ቃል ፡ አስቦ ፡ ወለደን። ፲፮፡ ስለዚህ ፥ የተወደዳችሁ ፡ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ ሰው ፡ ሁሉ ፡ ለመስማት ፡ የፈጠነ ፡ ለመናገርም ፡ የዘገየ ፡ ለቍጣም ፡ የዘገየ ፡ ይሁን ፤ ፲፯፡ የሰው ፡ ቍጣ ፡ የእግዚአብሔርን ፡ ጽድቅ ፡ አይሠራምና። ፲፰፡ ስለዚህ ፡ ርኵሰትን ፡ ሁሉ ፡ የክፋትንም ፡ ትርፍ ፡ አስወግዳችሁ ፥ ነፍሳችሁን ፡ ማዳን ፡ የሚችለውን ፡ በውስጣችሁም ፡ የተተከለውን ፡ ቃል ፡ በየዋህነት ፡ ተቀበሉ። ፲፱፡ ቃሉን ፡ የምታደርጉ ፡ ሁኑ ፡ እንጂ ፡ ራሳችሁን ፡ እያሳታችሁ ፡ የምትሰሙ ፡ ብቻ ፡ አትሁኑ። ፳፡ ቃሉን ፡ የሚሰማ ፡ የማያደርገውም ፡ ቢኖር ፡ የተፈጥሮ ፡ ፊቱን ፡ በመስተዋት ፡ የሚያይን ፡ ሰው ፡ ይመስላል ፤ ፳፩፡ ራሱን ፡ አይቶ ፡ ይሄዳልና ፥ ወዲያውም ፡ እንደ ፡ ምን ፡ እንደ ፡ ሆነ ፡ ይረሳል። ፳፪፡ ነገር ፡ ግን ፡ ነጻ ፡ የሚያወጣውን ፡ ፍጹሙን ፡ ሕግ ፡ ተመልክቶ ፡ የሚጸናበት ፥ ሥራንም ፡ የሚሠራ ፡ እንጂ ፡ ሰምቶ ፡ የሚረሳ ፡ ያልሆነው ፥ በሥራው ፡ የተባረከ ፡ ይሆናል። ፳፫፡ አንደበቱን ፡ ሳይገታ ፡ ልቡን ፡ እያሳተ ፡ እግዚአብሔርን ፡ የሚያመልክ ፡ የሚመስለው ፡ ማንም ፡ ቢኖር ፡ የእርሱ ፡ አምልኮ ፡ ከንቱ ፡ ነው። ፳፬፡ ንጹሕ ፡ የሆነ ፡ ነውርም ፡ የሌለበት ፡ አምልኮ ፡ በእግዚአብሔር ፡ አብ ፡ ዘንድ ፡ ይህ ፡ ነው ፤ ወላጆች ፡ የሌላቸውን ፡ ልጆች ፡ ባልቴቶችንም ፡ በመከራቸው ፡ መጠየቅ ፥ በዓለምም ፡ ከሚገኝ ፡ እድፍ ፡ ሰውነቱን ፡ መጠበቅ ፡ ነው።










Navigation menu

MediaWiki spam blocked by CleanTalk.